Logo
  • ethioexternalauditors@gmail.com
  • +251 941404142
News Photo

ኦዲት ባለሙያዎች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሙያዊ እውቀታቸውን ማሳደግ አለባቸው ተባለ

Ethiopian News Agency  · 

የኦዲት ባለሙያዎች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሙያዊ እውቀታቸውን ማሳደግ አለባቸው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦የኦዲት ባለሙያዎች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሙያዊ እውቀታቸውንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለፀ።

የውጭ ኦዲተሮች ማህበር ያዘጋጀው በኦዲትና በፋይናንስ ሪፖርት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተመሰከረላቸው ሂሳብ ባለሙያዎችና ኦዲተሮች የተሳተፉ ሲሆን በዘርፉ አለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ስርዓቶች በተመለከተ ማብራሪያም ተሰጥቷል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር እንዳሉት፥ ቦርዱ በዘርፉ ሙያዊ ስነምግባርና ነፃነትን ለማስጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ቦርዱ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ የሂሳብ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ለማስቻልና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለሙያዎች ተከታታይነት ያለው የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናዎችን አግኝተው ተወዳዳሪነታቸውን ለማሻሻልና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቦርዱ ፍቃድ የሚሰጥበትን መመሪያ በማሻሻል የፍቃድ አይነቶችን ማሳደጉን ጠቁመው፥ በዳይሬክተሮች ቦርድ ፀድቆ ወደፍትህ ሚኒስቴር የተመራ ደንብ መኖሩንም ተናግረዋል።

ቦርዱ የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅን ዓላማው አድርጎ እየሰራ እንደመሆኑ ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት።

የውጭ ኦዲተሮች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጌታነህ በበኩላቸው፥ ማህበሩ የኦዲት ድርጅት ያላቸው ከ130 በላይ አባላት እንዳሉት ተናግረዋል።

በፋይናንስ ሪፖርት ላይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስርዓቶች ትግበራ እንዳለ አንስተው፥ በኦዲት ዘርፍ የቴክኖሎጂ ስርዓቶችን ለማስፋት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በውጭ ያሉ ሶፍትዌሮች ላይ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ ቴክኖሎጂ የማበልፀግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኦዲት ሪፖርት ተዓማኒና ትክክለኛ እንዲሆን ለማስቻል ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ ባለሞያዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፋይናንስ ስርዓቱን እንዲያዘምኑ ጠይቀዋል።

የዛሬው መድረክ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መሆኑንና በቀጣይም መሰል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያ ዘቢባ አሊና የተመሰከረላቸው የኦዲት ባለሙያ ሀብታሙ ተስፋዬ በበኩላቸው በተለይ በኦዲት ዘርፍ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም መጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ውይይቱ ስራቸውን ለማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲገነዘቡ የሚያግዝ እንደሆነም ጠቁመዋል።

Share This News

Comment

Do you want to get our quality service for your business?